
በከተማዉ እያጋጠሙ ያሉ አደጋዎችን ለመቀነስ በሚደረገዉ ጥረት የሚዲያ ተቋማትና ባለሞያዎች ሚና የላቀ እንደሆነ ተገለፀ፡፡
የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በከተማዉ እያጋጠሙ ያሉ አደጋዎችን ለመቀነስ እየተደረገ ያለዉን ጥረት ለማገዝ የሚያስችል ዉይይት ከሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎችና ከሚዲያ ባለሞያዎች ጋር ዛሬ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ዉይይት አካሂዷል ።
የዉይይት መድረኩን የከፈቱት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ኮማንደር አህመድ መሀመድ እንደተናገሩት በአዲስ አበባ እያጋጠሙ ካሉ አደጋዎች የአብዛኛዎቹ የአደጋ መንስዔ በጥንቃቄ ጉድለት የሚከሰቱ በመሆናቸው እነዚህ በሰዉ ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እያደረሱ ያሉትን አደጋዎች የህብረተሰቡን የጥንቃቄ ባህል በማሳደግ አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል ጠቅሰው ለዚህም የሚዲያ ተቋማትና ባለሞያዎች ሚና የማይተካ በመሆኑ ከኮሚሽን መ/ቤቱ ጋር በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ሞላ በበኩላቸው እንደተናገሩት አደጋን አስቀድሞ በመከላከል ከተማዋን ሰላማዊና ከአደጋ የተጠበቀች ማድረግ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን አስታዉሰዉ የሚዲያ ተቋማትና የሚዲያ ባለሞያዎች ድርብ ኃላፊነት ያለባቸዉ በመሆኑ የአደጋ መከላከልን ጉዳይ በዘገባዎቻቸዉ በማካተት የህብረተሰቡ የጥንቃቄ ባህል እንዲያሳድጉ አሳሰበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ም/ቤት መሠረተ ልማትና ማዘጋጃ ቤታዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ግዛቸው አይካ መርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተዉ ባደረጉት ንግግር የአደጋ ስጋትን አስቀድሞ በመለየት ህብረተሰቡን ከማስተማርና ከማስገንዘብ አኳያ የዉይይት መድረኩ ወሳኝ እንደነበረ ጠቅሰዉ
ጋዜጠኞች የአደጋ ክስተትን መረጃ በሂደት ላይ እያለ እንዲሁም የአደጋዉን መነሻ ምክንያትን ከሚመለከተዉ አካል
አጣርቶ መዘገብ እንደሚገባቸዉም አስረድተዋል።
ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ በአደጋ ስጋት ቅነሳ ዘርፍ ኃላፊ በም/ኮሚሽነር ደሳለኝ ፉፋ ቀርቦ ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየት ቀርቦ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።
ለእሳትና ለሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም ለአንቡላንስ አገልግሎቶች በ939 ፈጥነዉ ያሳዉቁ