በአዲስ አበባ የሚገኙ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ኮሚሽን መ/ቤቱን እንዲያግዙ ጥሪ ቀረበ ።
በአዲሰ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት አስተባባሪነት በከተማዉ የሚገኙ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ከእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በትብብር ለመስራት በሚያስችላቸዉ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ጥር 5 ቀን 2017 ዓ.ም ዉይይት ተካሂዷል።
የዉይይት መድረኩን የመሩት በም/ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ እንደተናገሩት በሌሎች ሀገራት ባንክና ኢንሹራንሶች የእሳት አደጋ ተቋምን የሚያግዙበት አሰራር መኖሩን ጠቅሰዉ ኮሚሽን መ/ቤቱ ከተማዋን የሚመጥን አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችለዉ የሪፎርም ስራዎችን አቅዶ ወደተግባር የገባ በመሆኑ ይኸዉ የሪፎርም ስራ የተሟላ ዉጤት እንዲያስመዘግብ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ኮሚሽን መ/ቤቱን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍቅሬ ግዛዉ በበኩላቸዉ እንደተናገሩት ኮሚሽን መ/ቤቱ በጀመራቸዉ የሪፎርም ስራዎች በርካታ ዉጤቶችን ማስመዝገቡን ጠቅሰዉ ኮሚሽኑ አደጋን አስቀድሞ የመከላከል አቅሙ ሲጎለብት የሰዉ ህይወትና ንብረትን ከማዳኑ በላይ ባንኮችና ኢንሹራንሶችም አትራፊ እንደሚሆኑ አብራርተዋል።
በዉይይት መድረኩ ላይ ኮሚሽን መ/ቤቱ የከተማዋ ዕድገት መሰረት አድርጎ አሁን ያለዉ አቅምና አደረጃጀት ምን እንደሚመስል በም/ኮሚሽነር ይክፈለዉ ወ/መስቀል ሰፊ ገለጻ ተደርጓል።
በመድረኩ የተሳተፉት የባንክና ኢንሹራንሶች ስራ ኃላፊዎች እንደተናገሩት በከተማዉ የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ለመቀነስ በሚደረገዉ ጥረት የኮሚሽን መ/ቤቱን አቅም ማጠናከር የጋራ ኃላፊነታቸዉ መሆኑን ጠቅሰዉ በቀጣይ የሚኖሩ ዉይይቶችን መሰረት በማድረግ አስፈላጊዉን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አስታዉቀዋል።
ለእሳትና ለሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም ለአንቡላንስ አገልግሎቶች በ939 ፈጥነዉ ያሳዉቁ!