ኮሚሽን መ/ቤቱ ከሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለዉን የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ።
የአዲስ አበባ ከተማ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እና የሸገር ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት በአደጋ ቅነሳና በአደጋ ምላሽ ዘርፍ በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸዉን የስምምነት ሰነድ ዛሬ ህዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም ተፈራርመዋል ።
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሸገር ከተማ ም/ከንቲባ እና የአስተዳደርና አገልግሎት ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ጉግሳ ደጀኔ እንደተናገሩት የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በሸገር ከተማ በተለያዩ ክፍለ-ከተሞች አደጋዎች በአጋጠሙ ጊዜ ፈጥኖ በመድረስ በርካታ ሀብቶችን ከዉድመት በማዳን ላበረከተዉ አስተዋጾኦ ምስጋናቸዉን አቅርበዉ ኮሚሽን መ/ቤቱ በአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያለዉ በመሆኑ የዛሬዉ ስምምነት ሰነድ የሰዉን ህይወትና ንብረት እንዲሁም የጋራ የሆኑትን የልማት ስራዎቻችንና ከማናቸዉም አደጋ ለመጠበቅ የሚያስችል እንደሆነ አብራርተዋል።
የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ፍቅሬ ግዛዉ በኩላቸዉ እንደተናገሩት ኮሚሽን መ/ቤቱ በማናቸዉም ስፍራ ለሚያጋጥሙ ድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ በመስጠት ህይወትና ንብረት እየታደገ መሆኑንና በሸገር ከተሞች ላይ ተመሳሳይ አገልግሎቶችን ሲሰጥ መቆየቱን አስታዉሰዉ በዛሬዉ ዕለት የተንፈራምናቸዉ ስምምነቶች ተጨማሪ አገልግሎቶችን ያካተተ በመሆኑ ሁለቱም ከተሞች የጋራ ልማታቸዉን ከአደጋ ለመከላከል እንደሚያስችላቸዉ አብራርተዋል።
የስምምነት ሰነዱን በእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር በኩል ኮሚሽነር ፍቅሬ ግዛዉ የፈረሙ ሲሆን በሸገር ከተማ በኩል የሸገር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሮዛ መሀመድ ፈርመዋል።
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ በሸገር ከተማ የአስራ ሁለቱም ክፍለ-ከተሞች አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተገኝተዋል።
ለእሳትና ለሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም ለአንቡላንስ አገልግሎቶች በ939 ፈጥነዉ ያሳዉቁ!፡