በተጠናቀቀው የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ልዩ ልዩ የጤና እክልና አደጋ ለገጠማቸው 11025 ሰዎች የቅድመ ሆስፒታል ህክምናና የአንቡላንስ አገልግሎት እንደተሰጣቸው ተገለጸ፡፡
የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በአደጋ ምላሸ ዘርፍ ስር የሚገኙት የድንገተኛ አደጋዎችና የአደጋ ሰራተኞች ህክምና ዳይሬክቶሬት እና የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጣር ዳይሬክቶሬት ሰራ ክፍሎች የ2016 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸማቸውን አቅርበው በዘርፉ የሚገኙ የማዕከልና የቅርንጫፍ ጽ/ቤት አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ነሀሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ሪፖርት ቀርቦ ተገምግሟል ፡፡
በበጀት ዓመቱ በዘርፉ ከተከናወኑ በርካታ ስራዎች መካከል ልዩ ልዩ የጤና እክልና አደጋ ለገጠማቸው እንዲሁም ለነፍሰ ጡር እናቶች ቁጥራቸው 11025 ለሆኑ ሰዎች የነጻ የቅድመ ሆስፒታል ህክምናና አንቡላንስ አገልገሎቶች እንደተሰጣቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል ፡፡
በሌላ በኩልም በበጀት ዓመቱ በአዲስ አበባና አካባቢው 523 አደጋዎች አጋጥመው ህይወትና ንብረት ለማዳን በተከናወነ ተግባር ህይወታቸው አደጋ ውስጥ የነበረ 156 ሰዎችን መታደግ የተቻለ ሲሆን ከ 37 ቢሊየን ብር ባላይ የሚገመት ንብረትም ከውድመት ማዳን ስለመቻሉ በሪፖርቱ ቀርቧል ፡፡
የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍቅሬ ግዛው የግምገማ መድረኩን በከፈቱበት ጊዜ እንደተናገሩት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አደጋን ፈጥኖ የመቆጣጠር አቅማችን በማደጉ በሰውና በንብረት ላይ ሊደርስ የነበረን ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉን ጠቅሰው በከተማ ደረጃ በተከናወነውና እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ስራ ላይ የኮሚሽን መ/ቤቱ ባለሞያዎች ላደረጉት አስተዋጾ ምስጋናቸዉን አቅርበዋል፡፡
የግምገማ መድረኩን የመሩት ም/ኮሚሽነርና የአደጋ ምላሽ ዘርፍ ኃላፊ ኮማንደር መስፍን አያሌው በበኩላቸው እንደተናገሩት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የሰውን ህይወትና ንብረት ለመታደግ በሁለቱም ዳይሬክቶሬቶች በኩል የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው በበጀት ዓመቱ የታዩ ጠንካራ ጎናችንን አጠናክረን በመቀጠል ውስንነቶቻችንን በማሻሻል በቀጣይ በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ማሰመዘገብ እንድንችል ዝግጁነታችንን ማጠናከር ይገባናል ብለዋል ፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት በዘርፉ ሊከናወኑ በታቀዱ እቅዶች ላይ ሰፊ ውይይት ከተካሄደ በኃላ እቅዱ የጋራ ተደርጓል ፡፡
ለእሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም ለአንቡላንስ አገልግሎቶች በ939 ፈጥነው ያሳዉቁ