የኮሪደር ልማቱ በከተማዉ የሚያጋጥሙ የጎርፍ አ...

image description
- ሁነቶች fire disaster    0

የኮሪደር ልማቱ በከተማዉ የሚያጋጥሙ የጎርፍ አደጋዎችን ለመከላከል አስተዋጾ እያደረገ እንደሆነ ተገለጸ።

የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በአዲስ አበባ በጎርፍ አደጋ ምክንያት በሰዉና በንብረት ላይ እየደረሱ ያሉ አደጋዎችን ለመከላከል እንዲቻል እስከአሁን የተከናወኑ ተግባራትን የሚገመግም መድረክ ዛሬ ሀምሌ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ተካሂዷል።

በአዲስ አበባ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ተብለዉ በተለዩ ቦታዎች ላይ ኮሚሽን መ/ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያከናወናቸዉን ተግባራት የተመለከተ የዉይይት መነሻ ሪፖርት በም/ኮሚሽነርና በአደጋ ቅነሳ ዘርፍ ኃላፊ በአቶ ይክፈለዉ ወ/መስቀል ቀርቧል።

በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ስራ አሰኪያጅ ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ በመሩት በዚህ የግምገማ መድረክ ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸዉ ተቋማትና የክፍለ-ከተማ ስራ አስኪያጆች በጥናት በተለዩ ቦታዎች ላይ የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ ያከናወኗቸዉን ተግባራት በዝርዝር አብራርተዋል።

በዚህም ተቋማቱ ተጋላጭ ተብለዉ በተለዩ ቦታዎች ላይ ችግሩን ለማቅለል አዳዲስ የትቦ ቀበራ ፣ የድጋፍ ግንብ ስራዎች ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን ማጽዳት ፣ ተቆፍረዉ ክፍት የተተዉና ዉሀ ያቆሩ ጉድጓዶችን የመድፈን እንዲሁም ነዋሪዎችን ከቦታዉ የማስነሳትና ወደተሻለ ቦታ የማዛወር ስራዎች መከናወናቸዉን አስረድተዉ የኮሪደር ልማቱ እየተካሄደ ባለባቸዉ ቦታዎች ላይ የጎርፍ አደጋ ስጋት ለመቀነስ አስተዋጾ ማድረጉንም ጨምረዉ ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ ፍቅሬ ግዛዉ በበኩላቸዉ እንደተናገሩት በኮሚሽኑ ለአደጋ ተጋላጭ ተብለዉ በተለዩ ቦታዎች ላይ የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ላይ መሻሻሎች ቢኖሩም ያልተጠናቀቁ ቀሪ ስራዎች ተጠናቅቀዉ በሰዉና በንብረት ላይ ሊደርስ የሚችለዉን አደጋ ለመከላከል ቅድሚያ የሚሰጠዉ ጉዳይ እንደሆነም ተናግረዋል።

ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ በዉይይቱ ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት የጎርፍ አደጋ ስጋቱን ለመከላከል በየተቋማቱ የተከናወኑት ተግባራት የተሻሉ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንጻር የቀሩት ስራዎች ላይ የየተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮች ጭምር በልዩ ትኩረት ስራዉ ላይ መሳተፍ እንደሚገባቸዉ አሳስበዉ የከተማዉ ስራ አስኪያጅ ጽ/ቤት እስከአሁን ሲያደርግ የነበረዉን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታዉቀዋል።

በዉይይት መድረኩ ላይ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ፣ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ፣ የክፍለ-ከተማ ስራ አስኪያጆችና የኮሚሽን መ/ቤቱ ስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

ለእሳትና ለሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም ለአንቡላንስ አገልግሎቶች በ939 ፈጥነዉ ያሳዉቁ!